Monday, June 23, 2014



  • የመንበረ ፕትርክናው ነጻነት በተገኘበትና ብሔራዊ ቅዱስ ሲኖዶስ በተቋቋመበት ባለፈው ግማሽ ምእት በተነሡ ቅዱሳን ጥናትና አሠያየም ላይ ትኩረት ይሰጣል፡፡
  • ቀኖናው ተደጋጋሚ ራእይና ተኣምራት በማሳየት የተመሠረተውን የቤተ ክርስቲያናችንን የቅዱሳን አሠያየም ትውፊት ሲኖዶሳዊ በማድረግ የሚያጠናክር ነው ተብሏል፡፡
  • የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ አቡነ ቄርሎስ ስድሰተኛንና ሊቀ ዲያቆን ሐቢብ ጊዮርጊስን በቅድስና ለመሠየም በምታደርገው ዝግጅት ቅድስናቸውን ዐውቃላቸዋለች፡፡
  • ኹለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሐምሌ ቀን ፲፱፻፹፬ .. ‹‹ቴዎፍሎስ ቅዱስ ሰማዕት›› ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ በ፲፱፻፺፯ .. ‹‹ሰማዕተ ጽድቅ›› ተብለው እንዲጠሩ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዐዋጅ ወጥቷል፡፡
  • ወላዲተ አእላፍ ቅዱሳንቅድስት ኢትዮጵያ፡- በሰማይ በዐጸደ ነፍስ ተጋድሏቸውን ፈጽመው የጽድቅና የድል አክሊል ተቀዳጅተው የሚኖሩ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ሳይኾን በምድር በሕይወተ ሥጋ ከከሐድያን፣ ከመናፍቃን፣ ከፍትወታት እኩያትና ከኃጣውእ የሚጋደሉ የቃል ኪዳን ቅዱሳን አገርም ናት!
  •  
  • የቅዱሳን የፍጹምነትና የቅድስና ደረጃዎች
    የእግዚአብሔር ወዳጆች የኾኑ ቅዱሳን በአንድ ጊዜ የፍጹምነትና የፍጹምነትና የቅድስና ደረጃ ላይ አይደርሱም፤ ነገር ግን የተወለደ ሕፃን ቀስ በቀስ በመዳኽ ወደ መቆም፣ ከመቆም ወደ መራመድ ከዚያም መሮጥና መዝለል እንደሚጀምር ኹሉ ቅዱሳንም ከወጣኒነት ጀምረው በጸጋ እግዚአብሔር እየተጎበኙ ወደ ፍጹምነት ይደርሳሉ፡፡ ‹‹ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችኹ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ያበረታችኁማል፡፡›› እንዲል፡፡ (፩ኛጴጥ.÷፲፩)፡፡
    በወጣኒነት ጀምረው ፈተናውን እያሸነፉ ሲሔዱ በማዕከላዊነት ደረጃ አድርገው በመጨረሻ ከፍጹም ብቃት ላይ ይደርሳሉ፡፡ እነዚኽ ሦስቱ መንፈሳውያን ደረጃዎች፡- ወጣኒነት፣ ማዕከላዊነት እና ፍጹምነት ሲኾኑ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ እና ንጽሐ ልቡና በመባልም ይታወቃሉ፡፡ በዚኽም መሠረት ቅዱሳን ደረጃ በደረጃ የሚደርሱባቸው መዓርጋት በዝርዝራቸው ዐሥር ናቸው፡፡ እነዚኽም ሦስቱ በንጽሐ ሥጋ፣ አራቱ በንጽሐ ነፍስ፣ ሦስቱ በንጽሐ ልቡና ይገኛሉ፡፡